“አሳፋሪ ታሪክ እየሠሩ ረጅም ጊዜ ከመኖር፣ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ ሠርቶ በአጭር ጊዜ መሞት ይሻላል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

(ኅዳር 22/2018 ዓ.ም) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከደብረ ኤሊያስ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ( ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተደደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደብረ ኤሊያስ ወረዳ አሁንም የገዘፈ ችግር እንዳለ ገልጸዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ሲነሳ የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄ አስፈታለሁ ብሎ ነበር አሁን ግን ሕዝብን በግፍ እየገደለ እና እያሰቃየ ነው ብለዋል።

መነሻውም መዳረሻውም ለሕዝብ አለመኾኑን በግልጽ ማሳየቱንም ተናግረዋል።

ሰላማዊ ሰዎች በግፍ ተቀጥቅጠው ተገድለዋል፤ ሕጻናት ከእናታቸው እየተነጠሉ ተገድዋል ብለዋል።

ለእውነት የቆሙ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሠርተው የሚበሉ ነጋዴዎች፣ ሀገር የሚያለሙ ባለሀብቶች መሰደዳቸውንም ገልጸዋል።

እውነትን ይዘው፣ መስቀል አውጥተው ግፍን ያወገዙ እና የገዘቱ አባቶች ተገድለዋል ነው ያሉት።

ለትምህርት ቅድሚያ የሚሰጥ ማኅበረሰብ ከትምህርት ተነጥሎ መቆየቱንም ገልጸዋል።

ይሄን እያዩ ዝም ማለት የተገባ አይደለም፣ በአንድነት ተነስቶ መታገል ይገባል ነው ያሉት።

በጋራ ታጣቂ ቡድኑን ከአካባቢው ማጽዳት እንደሚገባም ተናግረዋል። ታጣቂ ቡድኑ የውጭ ተላላኪ ባንዳ መኾኑንም ተናግረዋል።

ባንዳ እና ጽንፈኛ መኾኑን ደብረ ኤሊያስ ላይ የፈጸመው በደል ትክክለኛ ማስረጃ ነው ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ የሃይማኖት አባቶች ጠንካራ እና እውነተኛ ኾነው ድርጊቱን ሊያወግዙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ በአንድነት ለሰላም እንዲሠራም አሳስበዋል።

ጽንፈኝነት እና ሽፍትነት ኢትዮጵያን አያሸንፋትም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በአንድነት ለሰላም በመነሳት ከሰላም እጦት መውጣት ይገባል ነው ያሉት።

ንጹሐን ሲገደሉ አይኾንም ይበቃል ብለው መነሳት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

የአካባቢው መሪዎች ሕዝብን አደራጅተው ሰላሙን እንዲጠብቅ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። የሃይማኖት አባቶች ታጣቂ ቡድኑን እንዲያጋልጡ አሳስበዋል።

አሳፋሪ ታሪክ እየሠሩ ረጅም ጊዜ ከመኖር፣ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ ሠርቶ በአጭር ጊዜ መሞት ይሻላል ብለዋል።

ሕዝቡን ከሥነ ልቦና ጫና፣ አካባቢውንም ከጽንፈኝነት ነጻ መውጣት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

አካባቢውን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top