(ኅዳር 22/2018 ዓ.ም) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ እና ሉማሜ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ከሁለት ዓመታት በፊት የተከሰተው ችግር ሕዝብን ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጎ መቆየቱን ተናግረዋል። ከተማ የሚኖረው ማኅበረሰብ ገጠር ከሚኖረው ማኅበረሰብ ጋር በሃዘን እና በደስታ እንዳይገናኝ፣ ነጋዴዎች እንዳይነግዱ፣ አርሶ አደሮች በተገቢው እንዳያመርቱ፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ አድርጓል ነው ያሉት።
የልማት ሥራዎች እንዳይቀጥሉ እና ወጣቶች ሥራ እንዳይፈጠርላቸው ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል። የታጠቀው ቡድን የባዕዳንን ተልዕኮ ለማስፈጸም ያደረገው ሙከራ በሀገር መከላካያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ ኃይል መስዋዕትነት ከሽፎ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ነው ያሉት።
አሁን ላይ የተሻለ ሰላም እና ልማት እንዳለም ተናግረዋል። የተጀመረውን ሰላም ለማስፋት እና ለማዝለቅ መወያየት እና በአንድነት መቆም ይገባል ብለዋል። እጃችን ላይ የገባውን ሰላም መጠበቅ ይገባናል ነው ያሉት።
ሰላም ጠል ኃይሉን መመከት እና መቃወም እንደሚገባም ተናግረዋል። አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። የተቋረጡ ልማቶችን ማስቀጠል እና ወደ ትምህርት ያልተመለሱ ተማሪዎችን መመለስ እንደሚገባም ተናግረዋል።
እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ሚገባን ከፍታ መሄድ ይገባናል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሁን ያለው ሰላም እንዲገኝ ላደረገው የሀገር መከላካያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት ሕዝቡ ለተጫወተው ሚናም ምስጋና አቅርበዋል። የሉማሜ ከተማ አሥተዳደር እና የአዋበል ወረዳ ነዋሪዎች ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመኾን የሠሩት ሥራ የሚያስመሰገን መኾኑን ነው የገለጹት።
አሁን የተጀመረው ሰላም አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ አርሶ አደሮች በነጻነት እንዲያመርቱ፣ ያመረቱትን ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ፣ ነጋዴዎች የንግድ ሥርዓቱን እንዲያሳልጡ እና ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲፋጠን መምከር ይገባል ብለዋል።
“ጉዳዩን የተገነዘበ እና የተደራጀ ሕዝብ ሲኖር ሰላም አስተማማኝ ይኾናል” ነው ያሉት። የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲቀጥሉ መመካከር እና የጋራ ግንዛቤ መያዝ እንደሚገባም ተናግረዋል። መንግሥት ከሚወጣው ሚና ባለፈ ሕዝቡ የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት ነው ያሉት።
ሕዝብ ተደራጅቶ አካባቢውን ካልጠበቀ ሰላም ዘላቂ እና የጸና አይኾንም ብለዋል። ሕዝቡ ከመደናገር ወጥቶ ራሱን እና አካባቢውን መጠበቅ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጫኑ።
Facebook https://www.facebook.com/share/1ZfJoPFYV7/
Ticktock https://www.tiktok.com/@amhara.region.pre?_r=1…
Telegram https://t.me/ANRS_PresidentOffice
Twitter https://x.com/AmGovernoffice/header_photo
You Tube https://www.youtube.com/@amhararegionpresidentoffic1192
WhatsApp https://whatsapp.com/channel/0029Vb6ZZXk1t90V1p2qyV03

