(ኅዳር 21/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በወቅታዊ የግብርና እና ገጠር ልማት ሥራዎች አፈጻጸምና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እያደረገ ነው።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ውይይቱ ያለፉ ሥራዎችን በመዳሰስ የቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
በግብርና ዋና ዋና አፈጻጸሞች እና የገጠር ኮሪደር ልማት ውይይት እንደሚደረግባቸው አንስተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግር በመቋቋም ልማት እየተፋጠነ መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የገጠመውን የሰላም ችግር በመቋቋም መልሶ ለማስተካከል እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን የተሠሩ የልማት ሥራዎች ተስፋ የተጣለባቸው ናቸውም ብለዋል።
ክልሉ የገጠመውን ችግር በስክነት በመወያየት ችግሩን ለመፍታት ውይይት ተደርጎ የ25 ዓመታት አሻጋሪ ፍኖተ ካርታ እና የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ መነደፉን ጠቅሰዋል።
እቅዱን ለመፈጸምም በትልቅ ቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል ዶክተር ድረስ።
የግብርናው ዘርፍ የክልሉን ምጣኔ ሃብት ግማሽ ድርሻ እንዳለው የገለጹት ዶክተር ድረስ የወረዳ መሪዎች የመጀመሪያ ሥራቸው ግብርና መኾኑን አመላክተዋል።
ድህነትን መታገያ መድረክ ግብርና መኾኑንም ገልጸዋል። ለዚህ ዘርፍ ሰኬታማነትም እንዲረባረቡም መሪዎችን አደራ ብለዋል።

