(ኅዳር 21/2018 ዓ.ም) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከደብረ ኤሊያስ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ( ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተደደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ባለፉት ዓመታት አስከፊ ችግር ሲገጥመን ቆይቷል፤ የሃይማኖት አባቶች ተገድለዋል፤ እውነት የተናገሩ ሞተዋል፤ ተው ያሉት ተሰቃይተዋል ነው ያሉት።
ሕዝቡ በስቃይ ውስጥ መቆየቱንም ተናግረዋል። ታጣቂ ቡድኑ ያላደረሰው ስቃይ የለም ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች በሃይማኖት ተቋማት እየተደበቁ ሕዝብን እያሰቃዩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ለወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥሩ ባለሀብቶች እየተሰቃዩ ከአካባቢው እየወጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ለሕዝብ ቆመናል ይሉናል፤ ነገር ግን በአሰቃቂ ሁኔታ ይገድሉናል፤ ልጆቻችን እንዳይማሩ ይከለክሉብናል፤ አርሰን እንዳንበላ ያደርጉናል ነው ያሉት። ከዚህ በላይ ይበቃናል፤ ሰላም እንዲመጣ በጋራ እንሠራለን ብለዋል።
ሰላምን የሰበከ እየታፈነ እየተገደለ መኾኑንም ተናግረዋል። በሃይማኖት እና በሕዝብ ስም የሚነግዱ የታጠቁ ኀይሎች ሕዝብን እያሰቃዩ ነው፤ መንግሥት በሃይማኖት ስም የሚነግዱትን፤ ሃይማኖት የማይፈቅደውን የሚሠሩትን አደብ ሊያስያዝቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።
የደብረ ኤሊያስ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሀብታሙ እሱባለው ደብረ ኤሊያስ ወረዳ በታጣቂ ቡድን ተነግሮ ያማያልቅ ግፍ የተፈጸመበት ወረዳ ነው ብለዋል። እውነት የተናገሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ንጹሐን በግፍ መገደላቸውን ተናግረዋል።
የሀገር ዋርካ የሆኑ ሰዎች ክፉ አካሄድን በመቃወማቸው ብቻ መገደላቸውንም ገልጸዋል። ለሃይማኖት አባቶች ፍትሕ ካልቆምን ለማንም ልንቆም አንችልም ነው ያሉት።
ሕዝቡ ላደረገው መስዋዕትነት ምስጋና አለን፤ ነገር ግን ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ አሁንም በጋራ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
መሪዎች ለአካባቢው ሰላም ሲሉ በሠሩ በግፍ መገደላቸውንም ተናግረዋል። በአካባቢው የተደራጀ ታጣቂ ቡድን ሕዝብን እያሰቃየ መኾኑንም ገልጸዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ እዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን በደብረ ኤሊያስ አካባቢ ሕዝብን ያማረረ ችግር መኖሩን ተናግረዋል። የሀገር መከለከያ ሠራዊት ለሕዝብ ሰላም እና አንድነት መስዋዕትነት እየከፈለ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሀገር መከለከያ ሠራዊት ለሃይማኖት፣ ለባሕል እና ለእሴት ጥንቃቄ ያደርጋል ያሉት አዛዡ የሃይማኖት አባቶች በሃይማኖት ተቋማት ላይ መሽጎ ሕዝብን እያሰቃየ ያለውን ኀይል በተሰጣቸው ሥልጣን ሊያወግዙትና በቃህ ሊሉት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ በቃህ ካለው እና ታጣቂውን ካጋለጠ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በአጭር ጊዜ የአካባቢውን ሰላም ያረጋግጣል ነው ያሉት።

