(ሕዳር 21/2018 ዓ.ም ) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከደብረ ኤሊያስ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ( ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ሕዝባችንን አንገት ያስደፋ ችግር ገጥሞን ቆይቷል ብለዋል። በተሠራው ሥራ አሁን ላይ በእጅጉ እየተሻሻለ የመጣ ሰላም ታይቷል ያሉት አሥተዳዳሪው ይሁን እንጂ አሁንም ማስተካከል የሚገባን ብዙ ጉዳይ አለ ነው ያሉት።
የደብረ ኤሊያስ ወረዳ ሕዝብ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መቆየቱን ተናግረዋል። ወረዳው ከራሱ በላይ ለሌሎች የሚያተርፍ ቢሆንም፤ በራሱ ልጆች እንዳያመርት፣ ልጆቹ እንዳይማሩ ተደርጎ ቆይቷል ብለዋል።
ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ፣ መምህራን እንዳያስተምሩ ኾነው መቆየታቸውን ተናግረዋል። በደብረ ኤሊያስ ወረዳ ከአማራ ሕዝብ ባሕልና እሴት ያፈነገጠ ድርጊት ሲፈጸም መቆየቱንም ገልጸዋል።
የአካባቢው ሕዝብ በራሱ ልጆች ሲሰቃይ መክረሙንም ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዳይመክሩ፣ እንዳያስታርቁ በጽንፈኛ ቡድኑ ሲሰቃዩ መኖራቸውንም ተናግረዋል። የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ማስፈን እንደሚገባም ገልጸዋል።
በዞኑ በርካታ ችግሮች ተፈጥረው ቢቆዩም አሁን ላይ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል። የሀገር መከለካያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ባደረጉት ተጋድሎ የተሻለ ሰላም መፈጠሩን አንስተዋል። የሀገር መከለካያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር የአካባቢው ማኅበረሰብ አሁንም የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የሰላም አማራጭ ክፍት ነው፤ የሰላም አማራጭን የሚቀበሉትን እንቀበላለን፣ የሰላም አማራጭን በሚገፉት ላይ የሕግ ማስከበር ርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ደብረ ኤሊያስ የሚታወቀው በሰላም ወዳድነቱ እና በአምራችነቱ ነው ብለዋል። ለሃይማኖት እና ለዘመናዊ ትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መኾኑንም ተናግረዋል።
ለሀገር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሊቃውንት የፈለቁበት፣ ለሀገር የሚበቃ ምርት የሚቀርብበት አካባቢ መኾኑንም ገልጸዋል። ይህ ሰላም ወዳድ እና አምራች ማኅበረሰብ አሁን ላይ ግን በጸጥታ ችግር ብዙ ዋጋ ከፍሏል ነው ያሉት። በደብረ ኤሊያስ የደረሰው የጸጥታ መታወክ የከፋ እንደነበርም ተናግረዋል።
አውዳሚ የኾነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እንደደረሰም ገልጸዋል። ንጹሃን በስቃይ እና በጭንካኔ የተገደሉበት አካባቢ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
አካባቢ ለልማት ትልቅ አቅም ያለው ቢኾንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ማልማት ሳይችል ቆይቷል ብለዋል። የደብረ ኤሊያስ አርሶ አደሮች እንዳያመርቱ፣ ምርታቸውን ለገበያ እንዳያቀርቡ እንግልት ሲደረግባቸው እንደቆየም ተናግረዋል።
የትምህርት እና የጤና ተቋማት ተዘግተው መቆየታቸውንም ገልጸዋል ። ማኅበረሰብን የሚያዋርድ ተግባር መፈጸሙንም ተናግረዋል። ከዚህ በላይ የሚደርስ ግፍ የለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ወጣቶች እና መላው ማኅበረሰብ ለሰላም በአንድነት መነሳት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል። ሰላም ወዳዱ እና ትርፍ አምራቹ አካባቢ ሲታወክ ዝም ብሎ ማየት እንደማይገባ አስገንዝበዋል ተናግረዋል።
የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማደረግ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በአንድነት እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።

