(ኅዳር 20/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የአራት ወራት የሥራ አፈጻጸም እና የአምስት ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ እየመከረ ነው።
በምክክሩ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ያለፈው ጊዜ እልህ አስጨራሽ የፈተና ዘመን ነበር ብለዋል።
አማራ ክልል በታሪኩ እንዳለፉት ሁለት ዓመታት ከውስጡ በወጡ ልጆቹ ተጠቅቶ፤ ያልተገባ መሰዋዕትነት ከፍሎ፤ ልጆቹ ከትምህርት እንዲነጠሉ ተደርጎ፤ ግብዓት እንዳይደርሰው፣ መንግሥታዊ አገልግሎት እንዳያገኝ የተደረገበት ዘመን አልነበረም ነው ያሉት።
በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ልማቱ ተጎትቷል፤ ኢኮኖሚው ተስተጓጉሏል፤ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ አድርጓል ብለዋል። ሕገ ወጥነት እና ዘረፋ እንዲነግስ ማድረጉንም አንስተዋል።
በተደረገው እልህ አስጨራሽ የፖለቲካ እና የሕግ ማስከበር ሥራ የጽንፈኛ ቡድኑ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ ደርሶበታል ነው ያሉት። ዕለት ከዕለት የመዋጋት አቅሙ እየተዳከመ ከተዋጊነት ወደ ሽፍትነት ተሸጋግሮ በየአካባቢው ሰው እንደሚያግት እና ገንዘብ እንደሚቀማም ተናግረዋል።
ጽንፈኛው ቡድን በሕግ ማስከበር ሥራው ከሚደርስበት ምት በተጨማሪ እርስ በእርሱ እየተገዳደለ መኾኑንም ገልጸዋል። አሁን ላይ የራሱን ሕይዎት ለማትረፍ የሚያስችል መውጫ ጠፍቶበት በጭንቅ ውስጥ ይገኛልም ብለዋል።
የጽንፈኛ ቡድኑን ማንነት እየዘገየም ቢኾን የተረዳው አብዛኛው ኀይል የሰላም ጥሪውን መቀበሉንም ተናግረዋል።
የፖለቲካ እና የጸጥታ መዋቅሩ ራሱን እያጠራ ሪፎርም እየሠራ ከሕዝብ ጋር በመወያየት የክልሉ ሰላም አሁን ወዳለበት ቁመና እንዲመለስ ሠርቷል ነው ያሉት።
የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ ኀይል በማሠልጠን ሰላም እንዲረጋገጥ መሠራቱንም ገልጸዋል። የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ ኀይሉ የማድረግ አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩንም ተናግረዋል።
የፖለቲካ እና የጸጥታ መሪዎች ፈተናን ወደ ዕድል እና ድል እየቀየሩ የባዳ እና ባንዳ ሴራን እየመከቱ የማይቀረውን ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። ሕዝቡን በልማት እና መልካም አሥተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያቆም ኀይል እንደሌለም ጠቁመዋል።
አሁንም ቢኾን ለሰላም የተዘረጋው እጅ አልታጠፈም ያሉት ኀላፊው ሰላምን የሚመርጡ ኀይሎችን አክብረን እንቀበላለን፤ የሰላም አማራጭን ትተው በውጊያ የመቀጠል ፍላጎት ያላቸውን እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።
በሚወሰደው የሕግ የማስከበር እርምጃ መላው ኅብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲሰጥ እና የተደበቁትን እንዲያጋልጥም አሳስበዋል።
የክልሉ የጸጥታ ኀይል ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር ለክልሉ ሰላም መሥራት እንደሚገባውም አመላክተዋል።
ሐሰተኛ መረጃ እያራገቡ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብረው የሚሠሩ፣ ክልሉ እንዳይረጋጋ፣ በልማት እንዲቀጭጭ የሚያደርጉ፣ ግጭት የሚቀሰቅሱ ኀይሎች ከጥፋታቸው እንዲታረሙ አሳስበዋል። በአንጻሩ ለሀገር መረጋጋት እና ሰላም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) በመስዋዕትነት በተገኘ ድል የሕዝብ ሰላም በአንጻራዊነት ተሻሽሏል ብለዋል። የሕዝብ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ሰላም እና ደኅንነትን ማረጋገጥ ይገባልም ነው ያሉት።
ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻለው ሰላም እና ደኅንነትን ማረጋገጥ ሲቻል ነው ብለዋል። የጸጥታ መዋቅሩ ከውጭ እና ከውስጥ የሚመጡ ጠላቶችን ለመመከት ክቡር መስዋዕትነት ከፍሏል ነው ያሉት።
የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች ከክብራችን ሊያወርዱን ያለ የሌለ ኀይላቸውን ተጠቅመዋል፣ ነገር ግን በክልሉ የጸጥታ ኀይል እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ችግሩ ተቀልብሶ ክልሉ ወደ አንጻራዊ ሰላም ተሸጋግሯል ነው ያሉት።
የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ሥራዎች በውጤታማነት እየተፈጸሙ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የጸጥታ ኀይሎች ለከፈሉት ክቡር መስዋዕትነት ክብር አለን ነው ያሉት። ሕዝብን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ እና የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት አሁንም ሥራ ይጠበቃል ብለዋል።
ታሪካዊ ጠላቶች እንዳሰቡት ሳይኾን እኛ እንዳሰብነው አስተማማኝ ሰላም መፍጠር አለብን ያሉት አስተባባሪው ወደ ተሟላ ልማት በመግባት ሕዝባችንን ተወዳዳሪ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት። የተሟላ ሰላም ማምጣት ከጸጥታ መዋቅሩ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት የጸጥታ መዋቅሩን ለማስተካከል ሪፎርም ሠርቷል ያሉት አስተባባሪው ሪፎርሞቹ ውጤት ማምጣት ጀምረው የተሻለ ሰላም መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት። የልማት ሥራዎችን በታሰበው ርቀት እና ጥልቀት ለመሥራት ወደ ተሟላ ሰላም መመለስ ይገባልም ብለዋል።
ኀይል ማሠባሠብ፣ ማሠልጠን፣ ማደራጀት፣ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ ይገባልም ብለዋል። ዕቅዶችን እና ግቦችን ለማሳካት ሰላም እና ጸጥታ ቁልፍ ጉዳይ ነው፤ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳይ ካዘነበለ ዕቅዶችን በተሟላ መልኩ ለማሳካት እንቅፋት ይኾናል ነው ያሉት። የጸጥታ መዋቅሩ ለሰላም እና መልካም አሥተዳደር መደላድል መፍጠር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

