የጤና መድኅን አገልግሎት አባላቱን በክብር እና በፍቅር የሚያስተናግድ መኾን አለበት።

(ኅዳር 19/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የማኅበረሰብ ጤና መድኅን አገልግሎት ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የጤና አገልግሎት ከመከላከል እና መቆጣጠር ጀምሮ በሽታዎች ሲክሰቱም በተፋጠነ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ እንዲኾን እየተሠራ ነው ብለዋል።

ጤና የሕይወት ዋጋ የያዘ እና ገበያ የማይገዛው ውድ ነገር ነው፤ ይህንን በውል መረዳት እና ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠትም ግድ ይላል ነው ያሉት።

ዘርፉ ከመንግሥትም ቁልፍ ተግባራት ውስጥ አንዱ እንደኾነም ጠቁመዋል። የጤና አገልግሎት ስንፈልግ የምንገዛው እና ሳንፈልግ ደግሞ የምንተወው ሳይኾን የግድ የኾነ ጉዳይ ነው ብለዋል።

መንግሥት ዜጎችን ከችግር ለመታደግ የሚያስችል ፍትሐዊ እና ተደራሽ የጤና ሥርዓት እንዲዘረጋም ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

በአገልግሎቱ ላይ የሚስተዋሉ የአቅርቦት ችግሮችን ለመፍታትም የጤና መድኅን አገልግሎት ተቀርጾ እየተሠራበት ነው ብለዋል። ይህም ጤነኛ እና አምራች ዜጋን ለመፍጠር ትልቅ ሚና እየተጫወተ መኾኑን አብራርተዋል።

ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት በተለይም የገጠሩን አካባቢ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እያደረገ ያለ ነው፤ የመንግሥት ሠራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ማኅበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎት ለመዘርጋትም በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ በሚገኘው ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉንም አመላክተዋል።

የጤና መድኅን ንቅናቄ ተግባር በርካታ ሕዝብ የሚንቀሳቀስበት እና በጊዜ የተገደበ በመኾኑ ከፍተኛ ቅንጅትን እና መተባበርን የሚጠይቅ መኾኑንም ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ በክልሉ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ይህ ውጤታማ እንዲኾንም መላው የክልሉ መሪዎች ከሕዝቡ ጋር በመኾን በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።

የሕዝቡ የጤና መድኅን አገልግሎት ፍላጎት እያደገ ቢኾንም አሁንም ድረስ ግን የሚጠበቀውን ያህል ሽፋን አልተሰጠም ብለዋል። ተገቢውን ሽፋን ለመስጠትም በዘርፉ የሚታቀፉ ዜጎችን ማብዛት፤ ለዚህም በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

“የጤና መድኅን ፍትሐዊ ብቻ ሳይኾን አባላቱን በክብር እና በፍቅር የሚያገለግል መኾን አለበት” ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በአባላት የሚነሱ የአገልግሎት ክፍተቶች በዚህ ዓመት እንደሚፈቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ያምሮት አንዱዓለም ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እየኾነ ነው ብለዋል። ከ63 ሚሊዮን በላይ ዜጎችም በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ኾነዋል ነው ያሉት።

በ2017 ዓ.ም ለጤና መድኅን 19 ቢሊዮን ብር መሠብሠቡንም ተናግረዋል። ይህ ገንዘብ ከአባላት፣ መክፈል ለማይችሉት ክልሎች ከመደቡት እና የፌዴራል መንግሥት የሰጠው ነው ብለዋል። ከዚህ ውስጥም ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚኾነው ከመንግሥት የተገኘ መኾኑንም ተናግረዋል።

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የክፍያ መጠኑ በየክልሎች የሚለያይ እና ፍትሐዊነት የጎደለው ነበር ብለዋል። ይህንን ለማስቀረትም እንደሀገር ውይይት ተደርጎ ሁሉም እንደየገቢ መጠኑ እና ፍትሐዊ በኾነ መልኩ እንዲያዋጣ እና አገልግሎቱን እንዲያገኝ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል ነው ያሉት።

ታካሚዎች በአገልግሎት ወቅት ችግር እንዳይገጥማቸው እና ጤና ተቋማትም ቀድመው አቅማቸውን እንዲገነቡ ለማስቻል ለተቋማቱ ቅድመ ክፍያ እንደሚፈጸምም ተናግረዋል።

የጤና መድኅን አባላትን መረጃ በጥራት በመያዝ አገልግሎቱን የማዘመን ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ጠቁመዋል። በአማራ ክልልም 150 ወረዳዎች የጤና መድኅን አባላትን መረጃ በዘመናዊነት እና በጥራት አደራጅተዋል ነው ያሉት።

አገልግሎቱ የበለጠ ተጠናክሮ የሕዝብ እርካታ ከፍ እንዲል አሁንም ቢኾን ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚጠይቁ የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሯ በተለይም በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች በትኩረት መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ጤናማ እና የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመገንባት መከላከልን እና አክሞ ማዳንን አጣምሮ የያዘ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ እየኾነ ነው ብለዋል። ዘላቂ እና የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፤ ይህ ተሳትፎም በማኅበራዊ የጤና መድኅን አገልግሎት የሚገለጥ መኾኑን ጠቁመዋል።

የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት በየጊዜው እየሰፋ እንደሚገኝ እና በ2017 ዓ.ም 80 ነጥብ 6 በመቶውን የክልሉን እማዎራዎች እና አባዎራዎች ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት እና የክልሉ መሪዎች ተሳትፎ ለዚህ ውጤት እንዳበቃም አብራርተዋል።

በአገልግሎቱ ላይ የሚነሱ ክፍተቶችን በመሙላት ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top