(ህዳር 3 ቀን 2018 ዓ.ም) ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ሥራ መጀመር በጣና ሐይቅ ሲሰጥ የቆየውን የትራንስፖርት አገልግሎት ይበልጥ በማዘመን የቱሪዝም ዘርፉን እያነቃቃ መምጣቱን በባሕር ዳር ከተማ በአስጎብኚነት የሚሰሩ ሰዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተው ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባን ሥራ በይፋ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።
የጀልበዋን ሥራ መጀመር በማስመልከት ኢዜኣ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ አስጎብኚዎች እንዳሉት፤ የጀልባዋ ወደ ሥራ መግባት በጣና ሐይቅ ላይ የነበረን ዘመኑን የማይመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት ቀይሮታል።
አገልግሎቱን በማዘመን ዘርፉን እያነቃቃው መምጣቱንም ነው የተናገሩት።
ከአስጎብኚዎቹ መካከል አቶ አበበ ያረጋል፤ የጀልባዋን ሥራ መጀመር በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማራው ማህብረሰብ በጉጉት ሲጠብቀው እንደቆየ ተናግረዋል።
ለቱሪስቶች በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኙ ታሪካዊና ባሕላዊ የመስህብ ሃብቶችን ለመጎብኘት ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በጣና ሐይቅ ዘመኑን በማይዋጅ፣ ምቾትና ፍጥነት በሌላቸው አነስተኛና ያረጁ ጀልባዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አዲሷ ጀልባ ፈጣን፣ ዘማናዊና ምቾት ያላት በመሆኗ በርካታ ጎብኚዎች ጀልባዋን ለመጠቀም ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሌላው በአስጎብኚነት ሥራ የተሰማሩት አቶ አበባው ሲሳይ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በርካታ ጎብኚዎች ባንድ ጊዜ ሲመጡ ለማስተናገድ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
የነበሩ ጀልባዎች አነስተኛና ውስን ሰው ብቻ እንደሚይዙ ጠቁመው፤ ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ብዛት ያለው ሰው የመያዝ አቅም ስላላት ችግሩ መፈታቱን ተናግረዋል።
ጀልባዋ ለጉዞ የሚያስፈልጉ ግብአቶች የተሟላላት በመሆኑ የጎብኚዎችን ቀልብ የመሳባ አቅሟ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
አቶ ኤፍሬም አብርሀም የተባሉ ሌላው አስጎብኚ፤ የጀልባዋ ስራ መጀመር በጣና ሐይቅ ለሚከናወነው የቱሪዝም ሥራ አዲስ መነቃቃት እየፈጠረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ሐይቁ የታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መስህብ ሃብት መገኛ በመሆኑ ይሄን ዘርፍ ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማዋል የጀልባዋ ሥራ መጀመር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጡ ከቆዩት ጀልባዎች በዘመናዊነቷ፣ በተገጠመላት ቴክኖሎጂ፣ በፍጥነቷና ለጎብኚዎች ባላት ምቾት ለየት ያለች መሆኗም ተመላክቷል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

