“ፋብሪካው ከዕለት ቀለብ ፍጆታ በዘለለ ግብዓት የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን የሚያፈራ እና የሥራ ባሕልን የሚቀይር ነው” ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

(ኅዳር 03/2018 ዓ.ም) በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የበቆሎ ምርት በግብዓትነት መጠቀም የበለጸገ የምግብ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል ፋብሪካ በደብረ ብርሃን ከተማ ተመርቋል።

በፋብሪካው ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ፋብሪካው ሀገር በቀል ሰብሎችን በመጠቀም የተመጣጠነ የምግብ ሥርዓትን ለማሻሻል የሚሠራ ነው ብለዋል።

በተለይም የበቆሎ ምርትን ዋነኛ ግብዓት በማድረግ ልዩ ልዩ የበቆሎ ምግቦችን፣ የህጻናት ምግብ እና የበቆሎ ዱቄትን በማምረት የአመጋገብ ባሕልን ከማሻሻል በተጨማሪ እንደ ሀገር ግዙፍ የኢኮኖሚ ምንጭ በሆነው የግብርና ምርት ላይ ያተኮረ መኾኑ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን የበለጠ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

“ሀገር የምትበለጽገው በእድልና በችሮታ ሳይኾን በጥረትና በታታሪ ትውልዶች አቅም ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ብራውን ፉድስ ፋብሪካ የመሥራትና የመቻል ብሎም የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና የበለጸገ የምግብ ሥርዓት በማቅረብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መኾኑን ተናግረዋል።

ፋብሪካው እንደ ክልል የኢኮኖሚ አቅም ከማጎልበት ባሻገር የፋብሪካዎች የግብዓት አቅርቦት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን ያስቀረና እዚህ ተመርቶ እዚሁ ወደ ፋብሪካ የሚገባ ምርት መጠቀሙ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

በተጨማሪም ይህ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የክልሉ የዘላቂ ልማት አካል በማድረግ ከዕለት ቀለብ ፍጆታ በዘለለ ለፋብሪካ ግብዓቶች የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ማፍራት እና የሥራ ባሕልን የሚቀይር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል እምቅ ሃብትና ሰፊ የሰው ኃይል ባለቤት በመሆኑ የግል ባለሃብቶችን በማስተሳሰር የሚፈለገውን የኢኮኖሚ ደረጃ ማምጣት ይቻላል ሲሉም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top