የኮምቦልቻ ከተማ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ እንዲፀድቅ የውሳኔ ሃሳብ መቅረቡ ተገለጸ፣

የኮምቦልቻ ከተማ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ እንዲፀድቅ የውሳኔ ሃሳብ መቅረቡ ተገለጸ፣

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 2ኛ አመት የስራ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2009 ዓ/ም ባደረገው አስራ ስምንተኛ መደበኛ ስብሰባ የኮምቦልቻ ከተማ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ እንዲያጸድቅ የውሳኔ ሀሳብ  ማቅረቡን ገለጸ፡፡

በአጀንዳው ላይ ውይይቱ የተጀመረው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ በሰጡት  ማብራሪያ ሲሆን የኮምቦልቻ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ረቂቅ የውሃ ታሪፍ በከተማ ውሃ አገልግሎቶች በኩል ተጠንቶና በቢሮው ታይቶ በመስተዳድር ምክር ቤቱ እንዲፅድቅ የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት የኮምቦልቻ ከተማ የውሃ ታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት አገልግሎት ጽ/ቤቱ ከመንግስት ድጎማ ሙሉ በሙሉ ተላቆ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ የሚያስችለው የኦፕሬሽንና ጥገና፣ የኢንቨስትመንት፣የመስመር ማስፋፊያና ማሻሻያ ወጭዎችን በራሱ እንዲሸፍን ለማስቻል፣ ውስን የሆነውን የመጠጥ ውሃ ሀብትን በአግባቡና በቁጠባ ለመጠቀም፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱን ዘላቂና አስተማማኝ በማድረግ የከተማዋን ህዝብ በማንኛውም ስዓትና ቦታ በቂና አስተማማኝ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እና ተቋሙ በተሟላና ብቃት ባለው ባለሙያ እንዲደራጅ  ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ዘላቂ ማድረግ እንዲቻል ነው ብለዋል፡፡

 

በዚህ መሰረት ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያዬ በኋላ የኮምቦልቻ የመጠጥ ውሃ  ታሪፍ  ማሻሻያ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ማስተካከያዎች ተደርገውበት ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

 

የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሰራተኞች የሲቪል ሰርቪስ ቀንን በደማቅ ሁኔታ ማክበራቸው ተገለጸ፡፡

የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሰራተኞች የሲቪል ሰርቪስ ቀንን በደማቅ ሁኔታ ማክበራቸው ተገለጸ፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሰራተኞች “በስነ-ምግባሩ የተመሰገነ ፐብሊክ ሰርቪስ ለኢትዮጵያ ህዳሴ” በሚል መሪ ቃል ሰኔ 21/2009 ዓ.ም የሲቪል ሰርቪስ ቀንን በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል፡፡

የመወያያ ጽሁፉን ያቀረቡት የጽ/ቤቱ የሰው ሀብት ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ንግስት አስፋው እንደገለጹት አገራችን ባለፉት 25 ዓመታት በኢኮኖሚ በማህበራዊ እና በፖለቲካው ዘርፍ ላስመዘገበችው ውጤት የሲቪል ሰርቫንቱ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን የመንግስት ሰራተኛው በጥልቅ ታህድሶው ራሱን አድሶ በስነ-ምግባሩ የተመሰገነ ሲቪል ሰርቫንት በመሆን ደንበኞችን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል፡፡ በቀጣይም አገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የሁሉም ሰራተኛ ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ይህንንም ከግብ ለማድረስ ሰራተኛው 12ቱን የስነ-ምግባር መርሆችን በመላበስ ህብረተሰቡን በቅንነት በታማኝነት ማገልገል አለበት ብለዋል፡፡ አያይዘውም አገራችን የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል የሲቪል ሰርቪሱ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በመልካም ስነ-ምግባር በመታነጽ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡


በሌላ በኩል ስብሰባውን የመሩት የዳያስፖራና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ማስሬ እንደተናገሩት ብቁና ውጤታማ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት ለክልላችንም ሆነ ለሀገራችን ህዳሴ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ  በመሆኑ ህዝብን በትህትና የሚያስተናግድ፣ ለህዝብ ጥያቄ ፈጣንና ፍትሃዊ ምላሽ የሚሰጥ፣ አሰራሩ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው የሰው ኃይል ሊኖረን ይገባል፡፡ በሲቪል ሰርቪሱ የሚንጸባረቁ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራት፣ሙስናና ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማስወገድ ክልላችን ብሎም ሀገራችንን ወደ ተሸለ የዕድገት ስልጣኔ ደረጃ ለማድረስ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ሰኔ 21/2009 ዓ.ም

የዳያስፖራና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

 

ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት

 

የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ማቋቋሚያ ደንብ መውጣቱ ተገለጸ

የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ማቋቋሚያ ደንብ መውጣቱ ተገለጸ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 2ኛ አመት የስራ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ/ም ባደረገው አስራ ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባ የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ማቋቋሚያ ደንብ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡

ውይይቱ የተጀመረው ሰብሳቢው ባቀረቡት ማብራሪያ ሲሆን አማራ ክልል በተፈጥሮ ሁሉም አይነት ምርት የሚመረትበት አካባቢ ቢሆንም ከፍራፍሬ ልማት አኳያ ትልቁ ችግር የዕውቀት ማነስ፣ የአቅርቦት ችግር ንፅህናው የተረጋገጠ ችግኞችን አዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ አለመቻሉ ሲሆን ይህንን ችግር ለመፍታት ቲሹ ካልቸር በማቋቋም ምርጥ የሆኑትን ዝርያዎች በላብራቶሪ በማባዛት ንፅህናው የተጠበቀና በአንድ ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን እያባዙ ለአርሶ አደሩ ዘር የሚሸጥና ከዚህ በተጨማሪም ለዩኒቨርስቲዎች መማሪያ የሚሆን ትልቅና ራሱን የቻለ የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ማቋቋም እንዳለበት ገልፀው የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብም ከህግ አኳያ ተገቢውን የህግ ቅርፅ እንዲይዝ ከማድግ አንፃር በህግ አማካሪያችን ታይቶ የቀረበ ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ በበኩላቸው ቲሹ ካልቸሩ በአመት ከ20 ሚሊየን በላይ ችግኝ ያባዛል ተብሎ በዕቅድ የተያዘ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አያይዘውም ችግኝ እያባዙ መሸጥ በጣም ትልቅ ሀብት የሚገኝበት የስራ መስክ እየሆነ በመምጣቱ በፍጥነት ባለቤት ኑሮት ወደ ተግባር መግባት አለበት የሚል አቅርበዋል፡፡

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በአሁኑ ሰዓት 82 በመቶ የሚሆነው ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን ለሁለትና ሶስት ወራት በኋላ ወደ ስራ መግባት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ቀሪ ስራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተደረገ መሆኑን ገልፀው ስራውን ለማጠናቀቅ ትልቅ ችግር የሆነው ባለቤት የሌለውና በተደራቢ ስራነት የተያዘ በመሆኑ በቀጣይ ይህ ትልቅ ፕሮጀክት ራሱን የቻለ የሚከታተለው አካል ኖሮት በበጀት አመቱ መጨረሻ አብዛኛው ስራ ተጠናቆ ስራ እንዲጀምር በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱም በቀረበው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን በማንሳት ሰፊ ውይይት ካካሔደ በኃላ የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል በተለይ አትክልትና ሆርቲ ካልቸርን  በማስፋፋት ግብርና ቢሮና አካባቢ ደንና ዱር እንስሳ ጥበቃና ልማት መስሪያቤቶች ሊሰሯቸው የሚችሉትን ስራዎች በማሳካት በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ፣ ለሀገር የሚጠቅምና ክልሉን ወደተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግር የሚችል ከፍተኛ ሀብት ማፍራት የሚችል ትልቅ ቲሹ ካልቸር በመሆኑ ራሱን የቻለ ማዕከል ሆኖ እንዲቋቋም በቀረበው ሀሳብ ላይ በመስማማት፤

ተጠሪነቱ ለግብርና ቢሮ እንዲሆንና የገቢ ምንጩን በተመለከተ በራሱ ገቢ የሚተዳደር ራሱን የቻለ ማዕከል ሆኖ ከመንግስት ድጋፍ የሚደረግለትና ከሌሎች ፍላጎት ካላቸው ወገኖች ጋር በስምምነት አብሮ እንደሚሰራ ፤

 

በአጠቃላይ የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ከማንም ጥገኛ ያልሆነ ራሱን የቻለ ማዕከል ሆኖ እንዲቋቋም የመስተዳድር ምክር ቤቱ ደንብ ሆኖ እንዲወጣ ወስኗል፡፡

 

የግንቦት 20 በዓልን ምክንያት በማድረግ በይቅርታ እንዲፈቱ ለህግ ታራሚዎች ውሳኔ መሰጠቱ ተገለፀ፡፡

የግንቦት 20 በዓልን ምክንያት በማድረግ በይቅርታ እንዲፈቱ ለህግ ታራሚዎች ውሳኔ መሰጠቱ ተገለፀ፡፡

አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 2ኛ አመት የስራ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ/ም ባካሔደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ ከ3000 (ሦስት ሽህ )በላይ የሚሆኑ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን ገለጸ፡፡

ውይይቱ የተጀመረው የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የክልሉን የይቅርታ ቦርድ የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ በማብራራት  ሲሆን በ2009 ዓ/ም የሚካሔደውን የግንቦት 20 የድል በዓል አስመልክቶ የ2ኛ ዙር የይቅርታ ተጠቃሚ በመሆን በክልሉ መንግስት ይቅርታ እንዲደረግላቸው በክልሉ ይቅርታ አቅራቢ ቦርድ ተጠንተው የተለዩ የህግ ታራሚዎች የይቅርታ መስፈርቱን አሟልተው ጥያቄ ካቀረቡት ታራሚዎች መካከል በየደረጃው በሚገኙ ሚኒ ካቢኔ ታይቶ በየቦርዱም የይቅርታ ጥያቄአቸው የተደገፉ በድምሩ 3275 ታራሚዎች በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ታይተው ለመስተዳድር ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ መሆኑን ገልፀው፣ በይቅርታ ቦርዱ ታይተው የውሳኔ ሀሳብ የቀረበባቸው የህግ ታራሚዎችን በዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ስለዚህ መስተዳድር ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት በማካሔድ እርቅ የማይጠይቁ የወንጀል አይነቶች ተከሰው የተቀጡ የእስራትና የባህሪ ለውጥ መስፈርቶችን ያሟሉ በየደረጃው በለው ሚኒ ካቢኔ ታይቶ የቀረበና እንዲፈቱ የቦርዱንም ድጋፍ ያገኙ ወንድ=2501 ሴት=69  ድምር=2570 ፤ በሰው መግደልና በመግደል ሙከራ ተከሰው የተፈረደባቸው ከሟች ቤተሰብ ወይም ከግል ተበዳዩ ጋር ታርቀው የዕርቅ ሰነድ ያቀረቡ በየደረጃው ያሉ ሚኒ ካቢኔ ያረጋገጠው የቦርዱንም ይሁንታ ያገኙ ወንድ 674 ሴት 6 ድምር 680 ፤ እርቅ በሚጠይቅ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉትና ለመታረማቸው ማረጋገጫ ቀርቦላቸው ነገር ግን ታራቂ ወገን በክልሉ ውስጥ የሌለ መሆኑ የተረጋገጠ ወንድ 20 ሴት 3 ድምር 23 ፤ በጤና መስፈርቱ መሰረት የማይድን የጉበትና የካንሰር ታማሚ የሆኑና ለዚህ ማረጋገጫ ያቀረቡ ወንድ 1 ሴት የለም ድምር 1 ፤ በእድሜ መስፈርት እድሜአቸው 86 አመትና ከዚያ በላይ የሆኑና እንዲፈቱ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ወንድ 1 ሴት የለም ድምር 1

 

በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱ አቅጣጫዎችንና ማስተካከያዎችን በማካተት ወንድ 3197 ሴት 78 ድምር 3275 የህግ ታራሚዎችን ከግንቦት 20 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ የይቅርታው ተጠቃሚ በመሆን ከእስር እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡

 

የአብክመ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መገምገሙ ተገለጸ

የአብክመ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት  የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መገምገሙ ተገለጸ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ግንቦት 09/2009 ዓ/ም የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገመገመ፡፡

የዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ጥሩ ውበት ጽ/ቤቱ ለ2009 ዓ/ም በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያከናወናቸው አንኳር ስራዎችን በዝርዝር ካቀረቡ በኋላ በልማት ሠራዊት ግንባታ በተደረጉ ውይይቶች በሰራተኛው ዘንድ የእውቀት፣ ክህሎት ፣የአመለካከት ለውጦች መታየታቸውንና የልማት ሥራዊት እንቅስቃሴ  በሙሉ ቁመና ላይ እንዲገኝ ውስንነት ያለባቸው የሥራ ክፍሎች የሥራ ማሳለጫ መሆኑን በመገንዘብ  ተጠናክሮ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ተሰማ ደምሴ ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ  ሰራተኛውን አወያይተዋል፡፡ ኃላፊው እንደገለጹት ባለፉት 9 ወራት ተቋሙና ዞኖች የለውጥ ስራዎችን በአግባቡ ለመፈጸም ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸው በቀጣይም በJEG መሰረት የተመደቡትን ሰራተኞች የዕውቀት፣የክህሎትና የአመለካከት ክፍተቶችን ለመሙላት የተለያዩ ስልጠናዎች መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ ጽ/ቤቱም አፈጻጸሙ ያለበትን ደረጃ የሚገልጽ መለኪያ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግና የጽ/ቤቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም ሰራተኛው ሪፖርቱን በዝርዝር ካዳመጠ በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን በመስጠት ግምገማው ተጠናቋል፡፡

አዘጋጅ፡-እንዳላማው ሞላ(የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ)

ግንቦት 09/2009 ዓ/ም

የዳያስፖራና ህዝብ ግንኙነት ይሬክቶሬት

 

ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት

 


Page 8 of 17
Content View Hits : 8340167

Comments

  • I'm so happy to read this. This is the kind of man...
  • Do người sử dụng đặt sửa máy giặt: https://mangdi...
  • It's the best time to make some plans for the futu...
  • Hello, the whole thing is going sound here and ofc...
  • Remarkable things here. I'm very satisfied to see ...

Latest News

Who is online

We have 26 guests online

Entertainment