በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የደረሰውን ጥፋት አስመልክቶ ከክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት (ካብኔ) የተሰጠ መግለጫ

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የደረሰውን ጥፋት አስመልክቶ ከክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት (ካብኔ) የተሰጠ መግለጫ

በክልላችን ሁለተናዊ ልማት ለማረጋገጥና ልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም የህዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዘርፈ ብዙ ተግባር በመንግስትና በመላው ህብረተሰብ የተቀናጀ ጥረት ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የሀገራችንንም ሆነ የክልላችንን ተስፋ ያለመለሙ ለውጦችና ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ ይህም ውጤት ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የራሱን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ መጥቷል፡፡ በቀጣይነትም ይህንኑ የህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግና ለማስፋት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው በመንግስት በኩል የህዝቡን እርካታ በሚፈለገው መጠን ያለማረጋገጥ ድክመቶች እየተፈታተኑን ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የህብረተሰቡ እርካታ እጦት ቅሬታ እና ብሶት ወደ ግጭት እያመራ ዋጋ እያሰከፈለን ይገኛል፡፡

ሰፊው የክልላችን ህዝብ የአገራችን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት በፈቀደለት መሠረት ከኋላ ቀርነት ተላቆ ከድህነት ለመውጣት በትጋት በሚረባረብበት በአሁኑ ወቅት ይህንኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴውንና የማህበረ ኢኮኖሚያዊ ልማት ግስጋሴውን የሚገቱ ፈተናዎች እየተደቀኑበት ነው፡፡ ሰሞኑን በክልላችን በተለይም በወልዲያና አካባቢዉ የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስና የሠላም መናጋት የክልሉን መስተዳድር ምክር ቤት በእጅጉ አሳስቦታል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ወልዲያ ከተማ ቀደም ሲል በወልዲያ እና በመቀሌ ከተማ የእግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡ ጥር 12 ቀን 2010 . የቃና ዘገሊላ በዓል በሚከበርበት ዕለት በበአሉ ታዳሚዎችና በህግ አስከባሪ አካላት መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋትና አካል መጉደል እንዲሁም የንብረት ውድመት የተከሰተ ሲሆን ውሎ ሲያድርም ግጭቱ በቆቦ እና መርሳ ከተሞች የቀጠለ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ አልፏል፡፡ ከሁሉም በላይ በወልዲያ፣በቆቦና በመርሳ ከተሞች ነዋሪዎች 13 ከፀጥታ ሃይሉ 2 በድምሩ 15 ወገኖቻችን ህይወት ማለፉ ከፍተኛ ሃዘንና ቁጭት ፈጥሮብናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ መስተዳድር ምክር ቤቱ ከሁሉ አስቀድሞ በጠፋው ውድና መተኪያ የሌለው የሰው ህይወት ከልብ የተሰማውን ጥልቅና መሪር ሃዘን እየገለፀ ለተጐጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ይመኛል፡፡

የተከሰቱ ግጭቶች መሠረታዊ መነሻ ምክንያቶቻቸው የህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ ጥያቄዎች እንዲሁም ቅሬታዎችና ብሶቶች መደማመርና ሳይፈቱ መዋል ማደራቸው ሲሆን በየደረጃው ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ ካለመስጠት ጋር የተያያዙም ናቸው፡፡ የክልሉ መንግስት በአሁኑ ወቅት እነዚህን ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ከምንጊዜውም በላይ ጥረት እየደረገና በትኩረት እየጠሰራ ይገኛል፡፡

የክልሉ መንግስት በወልዲያ ከተማ ጉዳቱ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ በልዩ ትኩረት በርዕሰ መስተዳድሩ መሪነት በቦታው በመገኘት ቅድሚያ የዜጐችን ህይወት ለመታደግና ግጭቱን ለማስቆም ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በጋራ ተረባርቧል፡፡ በዚህም የህብረተሰቡ ቀና እና አስተዋይነት የተሞላበት ተሳትፎ ተጨምሮበት አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህ ክስተት ከጥፋት ውጪ የሚገኝ አንዳችም ትርፍ ካለመኖሩም በላይ አንዳንዶቹ የግጭት አዝማሚያዎች የህዝቦችን ፀንቶ የኖረ አብሮነትንና አንድነትን በሚጐዳ መልኩ የተከሰቱ መሆናቸውና የመንግስት ተቋማትና የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ የዜጐች ሀብትና ንብረት በአጭር ጊዜ እንዲወድም አድርጓል፡፡ ይህ ሁሉ ክስተት ግን በምንም መንገድ ቢሆን ግጭቱ የተከሰተባቸውን የአካባቢ ህዝቦች የማይወክል ተግባር ነው፡፡

በዚህ ጥፋት ለህዝብ ጥቅም የተገነቡና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የኢንቨስትመንት እርሻዎች፣ የመንግስት ተቋማት እና ተሽከርካሪዎች ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ ሁሉም ውድመቶች በዚህ ዘመን ሊታዩ የማይገቡ አሳፋሪ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ግጭቱ የህግ የበላይነትን ከመጣሱ የተነሳ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ህይወት አናግቷል፤ ስጋትና ውጥረት እንዲነግስ አድርጓል፡፡

የአማራ ክልል ህዝቦች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሁሉም የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በፍቅር አብሮ የመኖር አኩሪ ባህልና ጥብቅ የሆነ ትስስርንና አብሮነትን ጠብቀው መኖርን የሚያውቁና በዚህም የሚገለፅ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ የእነዚህ እሴቶች ባለቤት የሆኑት የወልዲያና አካባቢው ነዋሪዎችም ግጭቶቹ ከተከሰቱ በኋላ በአካባቢው የህግ ጥሰትና ስርዓት አልበኝነት በመንገሱ የራሳቸውም ሆነ የመንግስት ሃብትና ንብረት ከዘረፋና ከጥፋት እንዲድን እንዲደረግ ለመንግስት ጥሪ ከማቅረባቸውም ባለፈ በሚችሉት አቅም ሁሉ የተጎዱትን ወገኖች በመደገፍና ከፖሊስ ጎን ሆነው ፀጥታውን በማስከበርና አጥፊዎችን ለህግ እንዲቀርቡ በመተባባር ላይ ናቸው፡፡

ከዚህ ሌላ በአካባቢው ግጭት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በቦታው በመገኘት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማወያየት ችግሮች በውይይትና በጋራ የሚፈቱ መሆናቸውን በመተማመን በአካባቢው የተፈጠረው ሁከት በአገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶችና በመላ ህብረተሰቡ ትብብር ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ የማድረግ ሥራ በመሰራት ላይ ነው፡፡ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በሰላም እና የህግ የበላይነት ጉዳይ ላይ መተማመን በመጀመሩ በአሁኑ ጊዜ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ለህግ እየቀረቡ ከተሞቹም ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ መግባት የጀመሩ ሲሆን መንገዶችም ተከፍተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

የክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት በተሻሻለው የብሄራዊ ክልሉ ህገ መንግስት አንቀፅ 56 ንዑሱ አንቀፅ (1) መሠረት የክልሉ ከፍተኛ አስፈፃሚ እና አስተዳደራዊ አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 58 ንዑስ አንቀፅ (6) እንደሚደነግገው መስተዳድር ምክር ቤቱ በክልሉ ውስጥ ህግና ስርዓት መከበሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ያለውን ወቅታዊ አቋም እንደሚከተለው አስቀምጧል፡-

1. በወልዲያ ከተማ ጥር 12 ቀን 2010 . የሃይማኖት ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅት የተፈፀመውን ድርጊት በሚመለከት ምንም እንኳን አንዳንድ ቡድኖች የሀይማኖቱ ስርዓት በማይፈቅደው መልኩ ተንኳሽ ተግባራት መፈፀማቸው ስህተት መሆኑን ብናምንም መነሻው ምንም ይሁን ምን የተፈፀመው የሰው ግድያም ሆነ በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የተደረገ ተኩስ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት በሚካሄድበት እና ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅትና ቦታ ፀጥታ ያደፈረሱም ይሁን በስነ-ስርዓቱ ታዳሚዎች ላይ ጥይት የተኮሱ፣ ሰው የገደሉ፣ ልዩ ልዩ ጉዳት ያደረሱ አካላት ጉዳዩ በዝርዝር ተጣርቶ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡

2. ጥር 12 ቀን 2010 . በወልዲያ ከተማ የደረሰውን ጉዳት መቃወምና በመሰለው መንገድ ማውገዝ ህገ-መንግስታዊ መብት ቢሆንም ይህንን በወልዲያ ከተማ የተፈጠረውን ግጭት በምክንያትነት በመጠቀም በዕለቱም ሆነ በተከታዮቹ ቀናት ዜጎች በያዙት አመለካከትም ሆነ ማንነታቸው ላይ በመመስረት የደረሰው ጥቃት ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ተግባር በመሆኑ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ኢንቨስትመት እንዲወድም የግለሰቦችና የመንግስት ሃብትና ንብረት እንዲቃጠል፣ እንዲዘረፍና በልዩ ልዩ መንገድ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ፣ በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያስተባበሩም ሆነ የተሳተፉ በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ በግጭቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ክህብረትሰቡ ጋር በመተባበር እንዲቋቋሙ ይደረጋል፡፡

3. በህብረተሰቡ የተነሱ በአመራር አካላት፣ በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በፍትሃዊ ተጠቃሚት የሚገለፁ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዝርዝር ተለይተው በቅደም ተከተል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡
4.
በወልዲያና በአካባቢው የተፈጠረው ግጭት ያደረሰው ጉዳት አሁን ከደረሰው በላይ እንዳይሆንና አድማሱን እንዳያሰፋ የፀጥታ ሃይሎች ያደረጉት ርብርብ የሚያስመሰግናቸው ሲሆን በታጋሽነትና በወገናዊነት ስሜት፣ የፀጥታውን ችግር ለመቅረፍ ለከፈሉት መስዋዕትንት እና ላደረጉት መልካም እንቅስቃሴ መስተዳደር ምክር ቤቱ ላቅ ያለ ምስጋናውን ይገልፃል፡፡

5. በወልዲያ፣ በቆቦ፣ በመርሳና በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡ በተለይም የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ያሳዩት ርብርብ አክብሮታችን ላቅ ያለ መሆኑን እየገለፅን በቀጣይም ህብረተሰቡን ሠላሙን ለማስከበርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደተለመደው ሁሉ ከክልሉ የፖሊስና የፀጥታና ሃይል ጐን ተሰልፎ እንዲንቀሳቀስ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በቀጣይም መንግስት የሰው ህይወት ያጠፉ፣ አካል ያጎደሉ እና ሃብት፣ ንብረት ያወደሙ ማናቸውንም ወገን መረጃ ላይ ተመስርቶ ከክልሉ በተወከሉ ሙያተኞችና አመራራሮች ደረጃ እያጣራ በመሆኑ ይህ እንደተጠናቀቀ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድና ይህንን በግልጽ ለህብረተሰቡ የሚሣውቅ መሆኑን ሲያረገግጥ የህብረተሰቡንም ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ አጥብቆ እንደሚሠራ በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡

በመሆኑም ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብም በየአካባቢው ከልማት ሥራው ሳይቋረጥ በአብሮነት መንፈስ የሰላም ባለቤትነት ተግባሩን ለአፍታም ቢሆን ሳይዘነጋ ከፀጥታ ሃይሉ ጐን በመቆም ሰላም ለማረጋገጥ እና የህግ የበላይነትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ በቀጣይነት እንዲወጣ አበክሮ ያሳስባል፡፡

ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም

የአማራብሔራዊክልላዊመንግስትመስተድድርምክርቤት

 

Last Updated on Wednesday, 07 February 2018 13:19
 

ለርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሰራተኞችና አመራሮች በስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱ ተገለጸ

ለርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሰራተኞችና አመራሮች በስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱ ተገለጸ

የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም  ለአመራሮችና ሰራተኞች በሥነ-ምግባር፣ ሙስናና የሙስና  ወንጀሎች ህግ በሚል ርዕስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን አስታወቀ፡፡

ከስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ወንጀል መከላከል ባለሙያ የሆኑት አቶ ሁነኝ ሰጣርገው  እንደገለፁት  ሥነ-ምግባር መልካም ፀባይ ወይም አድራጎት፤ በአንድ የሙያ መሥክ ከባለሙያው የሚጠበቅ አድራጐት ወይም አሠራር፣ መልካምም ሆነ መጥፎ ባህሪን የሚገልጽ ሲሆን ስነ ምግባር  ሁሉን አቀፍ የሆኑ መርሆዎች ሁሉም የሰዉ ልጆች  በግዴታና በሃላፊነት ማክበር ያለባችውና ይህም የተሻለ ህይወት ለመፍጠር አማራጥ የሌለዉ  ተግባር ነዉ ብለዋል፡፡

አቶ ሁነኝ ሰጣርገው አክለው እንደገለጹት ሙስናና የሙስና ወንጀል ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለልማት ፕሮግራም ስኬት እንቅፋትና የአለምን ሰላም የሚያናጋ ወንጀል መሆኑ የዓለምንም ሆነ የአገራችን ትኩረት የሚሻ ጉዳይ በመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሙስናን መከላከል ማለት ችግሮች እንዳይከሰቱ ባሉበት ማስቆም ማለት ሲሆን በዚህም መሰረት የባለስልጣኖችንና የመወሰን አቅም ያላቸውን ሰዎች ሀብት መመዝገብና መቆጣጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንም ሙስና ሰርተው ያገኛቸውን ግለሰቦች በተገኘው ጥቆማ መሰረት አጣርቶና መርምሮ ክስ በመመስረት ለፍርድ ቤት አቅርቦ እንደሚያስቀጣ አክለው ገልጸዋል፡፡

የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ ተሰማ ደምሴ በበኩላቸው ይህንን የተማርነውን ትምህርት ከራሳችን ስራ ጋር አዛምደን መስራት አለብን ይህ ተግባር ለአንድ ተቋም ብቻ የተሰጠ አይደለም ሁሉም ተባብሮ ችግሮችን መፍታት ይኖርብናል የሙስና ክትትሉ በእኛ መስሪያ ቤት በአሁኑ ሰዓት ጥሩ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ስለሆነ ሰራተኛው እንደራሱ ገንዘብ ቆጥሮ የጽ/ቤቱን ሀብትና ንብረት መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

 

 

 

የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት እንዴት መልማት እንዳለበት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አቅጣጫ አስቀመጠ

የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት እንዴት መልማት እንዳለበት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አቅጣጫ አስቀመጠ

የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን  ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው 11ኛ መደበኛ ስብሰባ የክልሉን የማዕድን ሀብት ልማት ለማሻሻል እንዲቻል የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቡን ገለፀ፡፡

የአማራ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ለገሰ እንደገለጹት የክልሉ የማዕድን ሃብት ልማት ውጤታማ በሆነ አሰራር ከተመራ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው ጠቀሜታ የጐላ ቢሆንም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኘው በርካታ የማዕድን ሀብት ልማት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንፃር የተለያዩ ውስብስብ ችግሮች እያጋጠሙ በመሆኑ በእነዚህ ችግሮች መባባስ ምክንያት የዘርፉ ልማት በህገ ወጥ የማዕድን ምርትና ዝውውር እየተሰናከለ የሚቀጥልበት ሁኔታ የተፈጠረ በመሆኑ ዘርፉን ለክልሉ ህዝብ ኢኮኖሚ ልማት ብሎም ለሃገራዊ ሶሽዮ- ኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት ተገቢውን ጥቅም ሊያመነጭ በሚችልበት ሁኔታ ከላይ እስከ ታች ያለውን አመራርና ፈፃሚ ባለሙያ በተግባርና በአስተሳሰብ ለማንቀሳቀስ እንዲቻል የንቅናቄ መድረኮች አስፈላጊ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱ በክልሉ ውስጥ ያለው የማዕድን ሃብት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ዘርፍ በመሆኑ በቀጣይ በአግባቡ ከመምራትና ከማስተዳደር አኳያ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ተግባሮች አስቀምጧል፡፡ ከተግባሮች መካከልም፡-ከጥናት ጋር በተያያዘና ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ኤጀንሲው በዋነኛነት በክልሉና በሀገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጥብቅ ተሳስሮ  መሰራት እንዳለበት፣ ስራው የብዙ አካላትን ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ በጀት ዓመት እንደ ትልቅ ስራ ተወስዶ ከክልል፣ ከሀገር፣ ከዩኒቨርስቲዎች ዕውቀቱ  ያላቸውን ሰዎች ያሳተፈ ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ እንዲዘጋጅ፣ ከከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናት ጋር ተያይዞ በዚህ ዓመት ኦፓል አምራች ከሆኑ ወረዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ህጋዊ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እንዲሰራና ስራውም በተወሰኑ ወረዳዎች እንዲጀመርና የእነዚህን ወረዳዎች አመራሮች ያቀፈ የንቅናቄ መድረክ እንዲፈጠር መስተዳድ ምክር ቤቱ አቅጣጫና ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

 

በአጠቃላይ የክልሉን የማዕድን ሀብት ልማት ለማሻሻል እንዲቻል በቀረበው መነሻ ሃሳብና በምክር ቤቱ በተሰጡ አቅጣጫዎች መሰረት ተግባሮች ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል እየተካሄደባቸው እንዲፈጸሙ መስተዳድር ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

 

የፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት በሚሻሻልበት ሁኔታ መስተዳድር ም/ቤቱ ውሳኔ አስተላለፈ

የፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት በሚሻሻልበት ሁኔታ መስተዳድር ም/ቤቱ ውሳኔ አስተላለፈ

የአብክመ ጤና ጥበቃ ቢሮ በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ለማሻሻልና መከናወን ስላለባቸው ተግባራትና በክልሉ ውስጥ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የተሰሩት ስራዎች በርካታ ችግሮችን እንዲፈቱ በዝርዝር ለመስተዳድር ም/ቤቱ አቅርቧል፡፡ነገር ግን በየአመቱ ወደ ሆስፒታሎች የሚሔደው ተገልጋይ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ብዙ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በዚህም መሰረት፡-

Ø ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የህክምና ትምህርት እየሰጡ ያሉበት ሆስፒታሎች ላይ ለአገልግሎት መስጫ የሚሆን ማስፋፊያዎችን በፕላናቸው ውስጥ አካተው እንዲሰሩ ለማድረግ ከዩኒቨርስቲዎች ፎረም ላይ መተማመን መድረስ እንደሚያስፈልግ፤

Ø በሪፈራል ሆስፒታሎች ተጨማሪ ማስፋፊያዎች እንዲኖሩ ፤

Ø በተለያዩ ምክንያቶች የወጡ ወጭዎች ለተቋማቱ የሚመላለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች፤

Ø በሪፈራል ሆስፒታሎች የመጀመሪያው የህሙማን ቅብብሎሽ አሰራር ሲጀመር የሚያጋጥመውን ግፊት ከወዲሁ በመገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፤

Ø ለፈለገ ህይወት ጊዚያዊ የሆነ በፍጥነት የሚደርስ ግንባታ ለእናቶችና ህጻናት ድንገተኛ ክፍል እንዲገነባ ማድረግ፣

Ø የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ማድረግ፣

Ø የአዲስ አለምን ሆስፒታል ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል ማሳደግ፣

Ø ተዘጋጅቶ በሚቀርበው የአገልግሎት መስጫ የዋጋ ተመን  እንደሚያስፈልግ ቤቱ አይቶ እንዲያፀድቅ በሚሉ ጉዳዮች መስተዳድር ምክር ቤቱ  ሠፊ ውይይት ካካሄደ በኋላ፡- በክልሉ ውስጥ በርካታ ሆስፒታሎች ተከፍተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ቢሆኑም የተገልጋዩ ፍሰት ማስተናገድ ከማይቻልበት ሁኔታ ላይ የመድረስ /የመጨናነቅ/ መድረስና በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ አየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በመረዳት ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግስት የሚቻለውን ሁሉ እንደሚደረግ መስተዳድር ም/ቤቱ ወስኗል፡፡

 

 

 

የላልይበላ አብያተ ፍልፍል ቤተ-ክርስቲያን ከፍተኛ ጥገና እንደሚያስፈልገው ተገለጸ፡፡

የላልይበላ አብያተ ፍልፍል ቤተ-ክርስቲያን ከፍተኛ ጥገና እንደሚያስፈልገው ተገለጸ፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 3ኛ ዓመት ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ቤተ መቅደሶችን ለማስጠገን ውይይት ማካሔዱን ገለጸ፡፡

ውይይቱ ሲጀመር የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኃላፊ የቅርሱ ጉዳት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው በእድሜ ብዛትና በሌሎች ተዛማች ምክንያቶች ቅርሶች የተገነቡበት አለቶች በመሰንጠቃቸው የተወሰነ ክፍላቸው ተቀርፍቶ የመውደቅና በስንጥቃቸው ወደ ውስጥ የዝናም ውኃ የማስገባት ሁኔታ ያለ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከዚህ በፊት የላልይበላ አለም አቀፍ ቅርሶች ከደረሰባቸው ከሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ጉዳቶች ማለትም ከዝናምና ከፀሀይ ለመከላከል ከ10 ዓመት በፊት በቤተማርያም፣ ቤተመድሀኒአለም፣ ቤተአባሊባኖስ፣ እና ቤተ አማኑኤል የተሰራው መጠለያ ክብደቱ እጅግ ግዙፍ ከመሆኑ በላይ እግሩ ከቅርስ ላይ የተቀመጠ እንጅ ከመሬት ጋር ተጣብቆ የታሰረ ባለመሆኑ ነፋስ የሚያወዛውዘው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም የመሬት እንቅስቃሴ ያለ መሆኑ የበለጠ የመሰነጣጠቅና የመፍረስ አደጋ እንዲጋረጥበት ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተለይም የቤተ ማሪያም የመጠለያው ቋሚዎች ያረፉት ከቤተ ጎልጎልታና ስላሴ ዋሻ አናት ላይ መሆኑ ችግሩን እጅግ አስከፊ መሆኑን በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ሁለተኛው አማራጭና ዘላቂ መፍትሔ ቤተ ገብርኤል እና ሩፋኤል ላይ የተሰሩ የጥገና እንክብካቤ ስራዎች መጠለያውን ከማውረዳቸው በፊት አብያተ ክርስቲያናት ላይ መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ የተዘጉ የመፍሰሻ ቱቦዎችና አረሞች የመልክዓ-ምድር የማስዋብ ስራዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሰራት  አለባቸው፡፡ በውቅር አብያተ ክርስቲያኖቹ ላይ የሚገኙትን የስንጥቅ መጠን ለማወቅ ክትትል ስለሚያስፈልገው ካሜራና ሌሎችም ደጋፊ መሳሪያዎች ያስፈልጋቸዋል፡፡

በአጠቃላይ ለቅርሱ ጥገናና እንክብካቤ የሚጠይቀው በጀት አንድ ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህንን መንግስት ብቻውን ስለማይችል የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እንዲሰራ የጥናት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

መስተዳድር ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ሠፊ ውይይት ካካሄደ በኋላ፣ የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት ሀብት የሀገር ቅርፅ እንደመሆኑ የፌዴራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባለቤት ሆኖ በትኩረት እየሰራው ያለና የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮም እንዲሁም የቤተክርስቲያኑ አካባቢ ህብረተሰብ በትኩረት እየሰራ በመሆኑ በተለያየ መንገድ ክልሉ መደገፍ እንዳለበት በመስማማት፣ እንደ ክልል  መደረግ አለበት በሚለው ላይ ማለትም፡- በሰው ጉልበት በቀላሉ ሊሰሩ የሚችሉትን የተዘጉ የማፋሰሻ ቱቦዎችና አረሞች፣ የመልከአምድር የማስዋብ ስራዎችና የመሳሰሉት በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲሰሩ ማድረግ፤ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ በጋራ በመነጋገር ከክልሉ የሚጠበቁ ማለትም ክልሉ ራሱን ችሎ ሊሰራቸው የሚገቡ ስራዎች ግልጽ ሆነው ተለይተው እንዲቀርቡ፤ በክልሉ መንግስት በኩል ለስራው የሚያስፈልግ በጀት መመደብ እንደሚኖርበት፣ በተለይ በቀጣዩ በጀት ዓመት ክልሉ በጀት በመመደብ ምን ሊሰራ ይችላል የሚለው በእቅድ ተይዞ በሚገባ ሊታይ እንደሚገባ በመግለጽ ክትትሉ ተጠናክሮ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ በኩል ሁልጊዜ ላሊበላን በተመለከተ የተሰራውን ለመስተዳድር ምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ተወስኗል፡፡

 


Page 3 of 17
Content View Hits : 8340212

Comments

  • I'm so happy to read this. This is the kind of man...
  • Do người sử dụng đặt sửa máy giặt: https://mangdi...
  • It's the best time to make some plans for the futu...
  • Hello, the whole thing is going sound here and ofc...
  • Remarkable things here. I'm very satisfied to see ...

Latest News

Who is online

We have 28 guests online

Entertainment